ግሪንላንድ ጠቅላላ ግንባታ በክልሉ ሲያከናውን የቆየውን የዓሳ ኩሬ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ የሳይት ርክክብ አድርጓል። ለዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከ35,000,000 (ሰላሳ አምስት ሚሊዮን) ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ክቡር አቶ መስረሻ በላቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ስራውን በይፋ ተረክበዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ክቡር አቶ መስረሻ በላቸው ድርጅቱ ላሳየው ታማኝነት እና አስተማማኝ አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ድርጅቱ ስራውን በገባው ቃል መሠረት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ በጥራት አጠናቆ ያስረከበ መሆኑንና የግንባታ ወጪውም ያለምንም አላስፈላጊ ብክነት በታቀደለት በጀት መከናወኑን ገልጸዋል። በተለይም የኩሬዎቹ ግንባታ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው በላቀ ደረጃ መገንባታቸውን ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል።
የግሪንላንድ ጀነራል ኮንትራክተር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አጥናፉ ሳህሌ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለርክክብ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። አቶ አጥናፉ አክለውም ድርጅታቸው መሰል የልማት ስራዎችን በጥራትና በታማኝነት በማከናወን ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ መሰረተ ልማቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ለማብቃት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህ ፕሮጀክት መጠናቀቁ ክልሉ በዓሳ ምርት እንዲያድግና ለማህበረሰቡም የተሻለ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
